መሪው ለገጣፎ ለገዳዲ በሜዳው ወሎ ኮምቦልቻን አስተናግዶ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።ለገጣፎ ለገዳዲዎች ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም አጀማመራቸው አመርቂ ያልነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመግባት በፋሲል አስማማውና ዘካርያስ ቱጂ አማካኝነት ወደ ግብ ተቃርበው ነበር።አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመከላከሉ ላይ ተጠምደው የታዩት ወሎ ኮምቦልቻዎች በ3ኛው ደቂቃ በብርሃኑ ኦርዴላ አማካኝነት ካደረጎት ብቸኛ ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል አጋጣሚዎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።ቀስ በቀስ ጨዋታው እየገፋ በሄደ ቁጥር በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተለይም በእንግዳው ቡድን ወሎ ኮምቦሎቻዎች በኩል የሀይል አጨዋወት አይሎ ተስተውሏል።በ35ኛው ደቂቃ አብዲሳ ጀማል የሞከረውን ኳስ የወሎ ኮምቦልቻው ግብጠባቂና አግዳሚው ተረዳድተው የመለሱበትን ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረው ልደቱ ለማ ቢያስቆጥርም የእለቱ ዳኞች ግቧን ከጨዋታ ውጭ በማለት ሳያፀድቋት ቀርተዋል። የለገጣፎ ተጫዋቾችና ደጋፊዎችም ውሳኔው ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውሏል።በቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ፋሲል አስማማው ሞክሮ በወሎ ኮምቦሎቻ ግብጠባቂ ከከሸፈበት ሙከራ ውጭ ተጨማሪ ሙከራ ሳንመለከት ተጠናቋል።በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ለገጣፎዎች ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ከጅምሩ ተጭነው መጫወት ሲችሉ ወሎ ኮምቦሎቻዎች በአንፃሩ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመሄድ በማሰብ በጥንቃቄ ተከላክለዋል።ለገጣፎዎች በፋሲል አስማማው ልደቱ ለማና አብዲሳ ጀማል አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም የወሎ ኮሞቦልቻው ግብጠባቂ አቡበከር ኑራ በሶስቱም አጋጣሚዎች በአስደናቂ ብቃት የሚቀመስ አልሆነም። በወሎ ኮምቦልቻዎች በኩል ሄኖክ ጥላሁንና ሀብታሙ ወርቁ አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።በጨዋታው ላይ ሌላው የተመለከትነው አስገራሚው ነገር ሰሞነኛ ድንቅ ብቃቱ ላይ የሚገውን የለገጣፎውን አጥቂ ልደቱ ለማን ለማቆም እግር በእግር እንዲከተለው ትዕዛዝ ተሰጥተቶት የገባው የወሎ ኮምቦልቻው ስለሺ ዘሪሁን ልደቱን ውሃ ለመጠጣት እንዲሁም የአሰልጣኝ ምክር ሊቀበል በሚሄድበት አጋጣሚ ጭምሮ ይከተልበት የነበረው መንገድ እጅግ አዝናኝ ነበር።
ዓድዋ ላይ ሶሎዳ ዓድዋ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በኃይልሽ ፀጋይ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ጎሎች አማካኝነት 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።
አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ደደቢት 3-1 አሸንፏል። ዘንድሮ ቡድን የተቀላቀለው ዘካሪያስ ፍቅሬ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ልዑልሰገድ አስፋው ተጨማሪዋን ግብ አስቆጥሯል። ለደደቢት ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ደግሞ አፍቅሮት ሰለሞን ነው።
ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ፌዴራል ፖሊስን 1-0 አሸንፏል። ረዘም ላለ ደቂቃ ያለ ግብ በተጓዘው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መገባደጃው ላይ ደሴዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በድሩ ኑርሁሴን ወደ ግብነት በመለወጥ ሶስት ነጥብ እንዲያሳኩ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው እንደተጀመረ የጦሳ ፈርጦቹ በርካታ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ወደግብ መቀየር ተስኗቸው ታይተዋል ።ደቂቃዎች በገፉ ቀጥር ጎል ፍለጋቸውን በአጥቂው በድሩ ኑር ሁሴን እና አክዌር ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉት ደሴዎች ወደግብነት መቀየር ሳይችሉ በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።ከእረፍት መልስ በአንፃሩ ፌደራል ፖሊሶች ተጠናክረው ገብተዋል። በ65ኛው ደቂቃ በተሰራው ጥፋት የእለቱ ዳኛ ለደሴ ፍፁም ቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ ፌደራል ፖሊሶች ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል ።ጨዋታውም ከ15 ያላነሱ ደቂቃዎችን ተቋርጧል ።የፌዴራል ፖሊስ ተጫዋቾች አንጫወትም ብለው ከእለቱ ዳኛ ጋር ግብ ግብ ሲፈጥሩ ታይቷል። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አጥቂው በድሩ ወደ ጎል ቀይሮ ደሴዎችን መሪ ማድረግ ችሏል ። ከጎሉ በኋላ በጣም የተነቃቁት ፖሊሶች የአቻነት ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ የደሴን የተከላካይ መስመር ሲያስጨንቁ ውለዋል ። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል ። ደሴ ከነበረበት 6ኛ ደረጃ ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል 4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ከመሪው ያለውን ልዩነትም ወደ 4 ዝቅ አድርጓል ።
ቢሾፍቱ ላይ ገላን ከተማ ከ ወልዲያ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
በጥምቀት በዓል ምክንያት ሜዳው በመያዙ የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና አቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።


