ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ|ወልዲያ ከተማ ከደሴ ከተማ

image

ትናንት በአንድ ጨዋታ የተጀመረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ጨዋታዎች ነገ በተለያዩ ከተሞች የሚደረጉ ሲሆን እኛም በሸህ ሙሀመድ ሁሴን አላሙዲን ስታዲየም ወልዲያ ደሴ ከተማን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል ።ከፕሪሚየር ሊጉ ከወረደ በኋላ በከፍተኛ ሊጉ እየተጫወተ የሚገኘው ወልዲያ ከተማ በወረደበት ዓመት ይመለሳል ተብሎ ቢጠበቅም አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተስኖት ለ2ኛ ጊዜ በከፍተኛ ሊጉ እየተጫወተ ይገኛል ።ባለፈው ዓመት ከወራጅ ቀጠናው በ 2 ደረጃ ከፍ ብለው ያጠናቀቁት እሳቶቹ ዘንድሮም ቢሆን ጥሩ አጀማመር አለማሳየታቸው በደጋፊው ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል። በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳቸው በፌዴራል ፖሊስ በሽንፈት የጀመሩት ወልዲያዎች አስከፊ ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ ። በብዙ የገንዘብ እና የአመራር ችግር የተከበበው ክለቡ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ የሚያስችል የተጫዋች ስብስብ የለውም። ገና ከስነ ልቦና ጫና ያልወጡት ተጫዋቾችም ለውጤት ቀውስ ዳርገውታል። ቡድኑ የሳሳ የተከላካይ ክፍል መያዙ ልክ እንደባለፋት ጨዋታዎች ነገም ለደሴ አጥቂዎች በቀላሉ ተጋላጭ መሆኑ የማይቀር ነው። በተመሳሳይም ጨራሽ የሆነ የፈጣን አጥቂ አለመኖርም ለክለቡ ፈታኝ ነገሮች ናቸው። እስካሁን በሜዳው ካደረጋቸው 3 ጨዋታዎች አንድ አሸንፎ በአንዱ አቻ ሲለያይ በአንዱ ደግሞ ተሸንፏል ።የቀድሞ ክለባቸውን የሚገጥሙት አሰልጣኝ አረጋይ ወንዲሙ ከሜዳ ውጭ ያለባቸውን ደጋማ ሪከርድ ለማሻሻል ፣ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ያለ ግብ ለረጅም ሰዓት በዘለቀው ጨዋታ ከደጋፊው የገጠማቸውን ተቃውሞ ለመካስ እና በወልዲያ ደጋፊዎች የሚደርስባቸውን ጥላቻ ለመቋቋም ነገ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣው የተከላካይ ክፍል ትንሽ እፎይታ የሚፈጥር ቢሆንም አሁንም ወሳኝ ግብ ጠባቂ አለመኖር ክለቡ ከሜዳው ውጭ ነጥብ ይዞ እንዳይመለስ አድርጎታል ። የወልዲያ የሳሳ የተከላካይ ክፍል ወደ ጎል በቀላሉ ለመድረስ ለማይቸገሩት የደሴ አጥቂዎች ጥሩ የማግባት እድልን ይፈጥራል ተብሎ ይገመታል ።ይሁን እንጂ ባለፉት 2 ጨዋታዎች ሽንፈትን ያላስተናገዱት እሳቶቹ ነገም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም ። በአጠቃላይ የነገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ቅኝቶቹ ደግሞ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት የሚያደርጉት ትንቅንቅ ትኩረት ስቧል።ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ሲገኙ በደሴ በኩል አማካዩ ተካልኝ በህመም ምክንያት ከቡድኑ ጋር ወደ ወልዲያ አልተጓዘም ።
የእርስ በርስ ግንኙነቶች
-በአድሱ የከፍተኛ ሊግ ፎርማት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ወልዲያ ላይ አቻ ሲለያዩ ደሴ ላይ ደግሞ ደሴ 1-0 አሸንፏል ።
-ወልዲያ 1 ጎል ሲያስቆጥር በአንፃሩ ደሴ 2 ጎሎችን አስቆጥሯል ።

Design a site like this with WordPress.com
Get started